የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያቤት ሠራተኞች በአገራዊ የድጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጅ ላይ ስልጠና እየተሰጠ ነው። የስትራቴጂ ሰነዱ ይዘት በትኩረት መስኮች፣ የትግበራ ሂደቶች ከሚጠበቁ ውጤቶችና ታሳቢዎች መነሻ ተደርጎ ለሠራተኞች ገለጻ ተደርጓል። ሠልጣኞች የስትራቴጂው መነሻዎች፣ ዝርዝር ይዘቶችና ግልጽነት ለሚያስፈልጋቸው ነጥቦች፣ ቅንጅታዊ አሠራሮችንና ለትግበራ ልንከተለው ስለሚገባ አካሄድ በማንሳት ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።ለሠራተኞች አስተያየትና ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአገራዊ የድጅታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬተር ጀነራል ዶክተር አብዮት ባዩ፥ “ስትራተጂው ከዚህ በፊት የደረስንባቸውን ስኬቶች በመንተራስ የወደፊቱን ለመተለም በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው። ስትራቴጅው ሲቀረጽ ከዚህ በፊት የደረስንባቸውን መልካም አፈጻጸሞችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በንጽጽር ቃኝቶ መነሻ አድርጓል። አሁን ማከናወን ካሉብንና ወደፊት ልንደርስበት ከሚገባው ደረጃ አኳያም በመተንተን ትኩረት አድርገን ለመስራት የምንችልባቸውን ጉዳዮች ለይተን እየሰራን ነው” ብለዋል።እንደ ዶክተር አብዮት ለስትራቴጅው ትግበራ ብዙ አገራዊ አቅሞች አሉን። ለትግበራው የሕግ ማዕቀፍ፣ ቅንጅታዊ አሰራርና የተማረ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው። ከሕግ አውጭውና አስፈጻሚው በኩል መነሳሳት መኖሩን አውስተው ከተማረ ኃይል አኳያ ብዙ ወጣት ኃይል በትምህርት ቤትና በልዩ ልዩ መስኮች ተሰማርቶ ይገኛል።በአሁኑ ወቅት ከአገራችን ሕዝብ ብዛት 26 ሚሊዮን ያክል ወጣት በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል። ከትምህርት ውጭ ያለው ዜጋም ለድጅታል ቴክኖሎጂ በአንድም በሌላም ቅርበት ያለው ነው። ይህን አቅም አቀናጅተንና አስተባብረን ከተገበርነው በአጭር ጊዜ ውጤት በማምጣት የአገራችንን ኢኮኖሚ ማገዝ እንችላለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍና የ10 ዓመት ዕቅድን ለመተግበር በሚችል መልኩ እንዲፈጸም በስትራተጅው ይዘትና ጠቀሜታ ግንዛቤና ግልጽነት ለመፍጠር ከትምህርት ተቋማትና ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ስለሚገባ ስራው እንደተጀመረ ተብራርቷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሐብትና አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አባይነህ ሙሉጌታ በበኩላቸው ለስትራቴጅው ትግበራ ከአገራዊ አቅሞች በተጨማሪ የሚኒስቴር መስሪያቤታችን ሠራተኞች የመሪነት ሚናቸውን የጎላ ነው። የተቋሙ ሠራተኛ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን የምናደርገውን እንቅስቃሴ በንቃት ሊደግፍና ሊያግዝ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

Leave a Comment